በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኘው ስዋንሲ ሲቲ አሰልጣኝ ፖል ክሌመንትን አሰናብቷል።
ክለቡ በዘንድሮ የውድድር ዘመን እስካሁን ከተደረጉ 18 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሶስቱን ብቻ ሲሆን ሶስት አቻ ተለያይቷል፤ በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ደግሞ ሽንፈትን አስተናግዷል።
በዚህም 12 ነጥቦችን ብቻ በመያዝ 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የ45 ዓመቱ ተሰናባቹ ፖል ክሌሜንት የስዋንሲ አሰልጣኝ የሆኑት ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ነበር።
ባለፈው የውድድር ዓመት ክለቡን እንደያዙ ከነበረበት የወራጅ ቀጠና አውጥተው 15ኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ አድርገዋል።
የክለቡ ሊቀመንበር ሁው ጀንኪንስ፥ አሰልጣኙን መቀየር የፈለግነው ክለቡን ከወራጅ ቀጠና ለማውጣት ያለን የመጨረሻ አማራጭ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ስዋንሲ ምክትል አሰልጣኞቹ ኒጌል ጊብስ እና ካርል ሃላቢ ክለቡን መልቀቃቸውን አስታውቋል።
የዌልሱ ክለብ በ24 ሰዓት ውስጥ የአሰልጣኝ ክፍሉን እንደሚተካ ገልጿል።
አሰልጣኝ ክሌመንት ስዋንሲን ከመቀላቀላቸው በፊት በቼልሲ፣ በፓሪስ ሴንት ጀርሜይን እና በሪያል ማድርድ የካርሎ አንቼሎቲ ምክትል አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል።
በድርቢ ካውንቲ የነበራቸው አጭር የአስልጣኝነት ቆይታ በ2016 በማብቃቱ ተመልሰው በባየር ሙኒክ የአንቼሎቲ ምክትል ለመሆን ተገደዋል።
ከዚያም የስዋንሲ አሰልጣኝ ሆነው የሁለት ዓመት ከግማሽ ውል ቢፈራረሙም አንድ ዓመት እንኳ ሳያገለግሉ ተሰናብተዋል።
ምንጭ፦ቢቢሲ

ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ