ማክሰኞ 17 ዲሴምበር 2019

#ቦይንግ ከደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርትን በጊዜያዊነት ሊያቋርጥ መሆኑን አስታውቋል።

እንደ ኩባንያው ገለፃ የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርት ከፊታችን ጥር ወር ጀምሮ በጊዜያዊነት የሚቆም መሆኑ ታውቋል።

የኩባንያው ቦርድ ለሁለት ቀናት በአሜሪካ ቺካጎ ከተወያየ በኋላ ነው የአውሮፕላን ምርቱ እንዲቆም ውሳኔ ያሳለፈው ተብሏል።

ይህ የሆነውም የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ከአውሮፓውያኑ 2020 በፊት አውሮፕላኖቹ ወደ በረራ እንዲገቡ ፍቃድ አልሰልጥም ማለቱን ተከትሎ ነው።

የቦይንግ ምርት በሆኑት 737 ማክስ አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዢያ በደረሰ አደጋ በድምሩ የ346 ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትትሎ ካሳለፍነው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ከአገልግሎት ውጭ ተደርገው መቆማቸው ይታወሳል።

ሰኞ 16 ዲሴምበር 2019

#ፎርብስ መፅሔት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ከዓለማችን 100 ተፅእኖ ፈጣሪ ሴቶች አንዷ አድርጎ መረጠ፡፡ ፕሬዝዳንቷ በ2019 የአፍሪካ ብቸኛዋ ተመራጭ ናቸው፡፡


መፅሔቱ ለያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ባወጣው የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅን በ93ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧቸዋል፡፡
መፅሔቱ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በአፍሪካ ብቸኛዋ በስልጣን ላይ ያሉ ሴት የአገር መሪ እንደሆኑ አስፍሯል፡፡
ፕሬዝዳንቷ ወደዚህ ታላቅ ኃላፊነት በተሾሙ ጊዜ ለህዝብ እንደራሴዎች ባደረጉት ንግግር የሴቶች ድምፅ ለመሆን ቃል መግባታቸውንና የአንድነትን አስፈላጊነት አስረግጠው መናገራቸውን መፅሔቱ አስታውሷል፡፡
የጀርመኗ መራሄተ መንግስት አንጌላ መርክል፣ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ መሪ ክርስቲያን ላጋርድ እንዲሁም የዩናይትድ ስቴት ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ደረጃ እንደያዙ መረጃው አመልክቷል፡፡

ማክሰኞ 10 ዲሴምበር 2019

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ተቀበሉ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማታቸውን ተቀበሉ።

የኖቤል የሰላም ሽልማት ስነ ስርዓት በዛሬው እለት በኖርዌይ ኦስሎ በመካሄድ ላይ ይገኛል ።

በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።

ባለፈው መስከረም 30 በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።

ዶክተር ዐቢይ ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀው የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ኮሚቴው መግለፁ የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም ሁሉም ባለደርሻ አካለት በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሰላም እና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋፀኦ እውቅና ለመስጠትም እንደተመረጡ ኮሚቴው ገልጿል።

ኮሚቴው በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማምጣት ቃል መግባታቸውን በማስታወስ፥ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበል ሀገራቱ አስመራ ላይ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ማስቻላቸውን ነው ያነሳው።

ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ስምምነት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻክሮ የነበረው የጅቡቲና ኤርትራ ግንኙነት እንዲስተካል ሚና እንደነበራቸው አስታውሷል።

የኖቤል ኮሚቴው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለረጅም አመታት የነበረው ውጥረት እንዲፈታ ተነሳሽነት ሲወስዱ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ሀሳቡን በበጎ መልኩ ተቀብለዋል ብሏል።

ከዚህ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ በርካታ ለውጦችን በመካሄድ የሀገሪቱ ዜጎች ለተሻለ ህይወት ተስፋ እንዲያደርጉ አድርገዋል ብሏል ኮሚቴው።

ሰኞ 9 ዲሴምበር 2019

የታህሳስ ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ባለበት የሚቀጥል መሆኑን የኢፌዴሪ ንግድ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።


ሚኒስቴሩ በላከው መግለጫ ፥የአውሮፕላን ነዳጅ መሸጫ ዋጋ ከባለፈው ወር ሲሸጥበት ከነበረው  ጭማሪ ማሳየቱን አስታውቋል።
በዚህ መሰረትም የአውሮፕላን ነዳጅ በህዳር ወር ሲሸጥበት ከነበረው በሊትር 24 ብር ከ87 ሳንቲም በዓለም ወቅታዊ ዋጋ መሰረት ተሰልቶ በተገኘው ልዩነት 3 ብር ከ37 ሳንቲም በጨመር በሊትር 28 ብር 24 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል።
ከዚህ ውጭ ሌሎች የነዳጅ ምርቶች ዋጋ በታህሳስ ወርም በነበረበት እንዲቀጥል የተወሰነ መሆኑን ነው የገለጸው።
በዓለም ገበያ ላይ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ እንደአስፈላጊነቱ ማስተካከያ ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ሚኒስቴሩ አሳስቧል።