እሑድ 24 ዲሴምበር 2017

የሞባይል ስልክ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ነው ► የብረት አቅርቦት ይሻሻላል

የሞባይል ኢንዱስትሪው ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከ14 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘቱን የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ። የአርማታ ብረት ጥሬ ዕቃ ወደ አገር ውስጥ እየገባ በመሆኑ የብረት አቅርቦት ሊሻሻል እንደሚችል ተገልጿል።
የኢንስቲትዩቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በቀለ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 12 የሞባይል ስልክ ማምረቻ ኩባንያዎች አሉ። በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙት እነዚህ ኩባንያዎች የአገር ውስጥ ገበያን አሟልተው ምርቶቻቸውን ወደውጭ ኤክስፖርት በማድረግ 14 ሚሊዮን488ሺ 775 ዶላር ገቢ አስገኝተዋል።
የኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ዘርፉ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ወቅት ላይ ማቆጥቆጥ ጀምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ዕድገት ማሳየቱንና አገራዊ ኢኮኖሚውን በመደገፍ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ዘርፉ 16ሚሊዮን 969ሺ 72 ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ ከፍተኛውን የኤክስፖርት ድርሻ የያዘው የሞባይል ስልክ ሽያጭ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሄ የሞባይል ስልክ ምርት ኤክስፖርት የሚደረገው በቴክኖሎጂ ከኢትዮጵያ ሻል ብለው በሚገኙ አገራት ጭምር መሆኑን የተናገሩት አቶ ፊጤ ፣ከነዚህም መካከል ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳን ጨምሮ ሰባት የአፍሪካ አገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ።
በኢንቨስትመንቱ ከተሰማሩ ከ12ቱ ኩባንያዎች መካከል አራቱ የአገር ውስጥ ሲሆኑ፣ አብዛኛቹ የውጭ ኩባንያዎችና በሽርክናም የሚሰሩ ናቸው።ኩባንያዎቹ በአገር ውስጥ እሴት ጨምሮ በመገጣጠም ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ። እንደ ኩባንያዎቹ አቅም የፈጠሩት የሥራ ዕድል የተለያየ ቢሆንም ከአንድ ሺ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።ተቀጣሪዎቹ ወጣቶች በመሆናቸው ደግሞ ከሥራ ዕድሉ በተጨማሪም ቴክኖሎጂውን በመቅዳት ለነገ እያስቀሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተያያዘም በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ምክንያት ለዘጠኝ ወራት ተይዞ የነበረው የአርማታ ብረት የጥሬ ዕቃ ግዢ ችግር መፈታቱን አቶ ፊጤ አስታውቀዋል።ባለሀብቶቹ ጥሬ ዕቃ መግዛት ባለመቻላቸው በብረት ምርት አቅርቦት እና ዋጋ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ፈጥሮ እንደነበር ገልጸው ፣መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ እና የውጭ ምንዛሪም በመገኘቱ ምክንያት አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃውን ማስገባት መጀመራቸውን ተናግረዋል። የብዙዎቹ ደግሞ ወደብ ላይ ደርሷል። የጥሬ ዕቃ መግባት የብረት ምርት እንዲመረትና በገበያ ላይ ያለው እጥረትና የዋጋ ንረት እንዲሻሻል የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአገሪቱ የሚገኙ የብረት ኢንዱስትሪዎች በዓመት ከአምስት ሚሊዮን ቶን በላይ ብረት የማምረት አቅም እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን (አልማዝ አያሌው)

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ