በገበያ መር ኢኮኖሚ ገበያውን የሚቆጣጠሩት ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ይልቅ ሁለቱ ዋና ዋና ኃይሎች (Market forces) ፍላጎትና አቅርቦት እንደሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በነፃ ኢኮኖሚ መርህ አምራቾች ምን እና በምን ያህል መጠን ማምረት እንዳለባቸው እንዲሁም ያመረቱትን ምርት በምን ያህል ዋጋ መሸጥ እንዳለባቸው ራሳቸው ይወስናሉ፡፡ ውሳኔያቸው ደግሞ በውድድር፣ አቅርቦትና ፍላጎት ተፅዕኖ ስር ነው፡፡
ይሁንና መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን በበለጸጉ አገራት ጭምር ያልተገባ የግብይት ስርዓት እንዳይከሰት መንግስት በተመረጡ መስኮች ላይ ጣልቃ ይገባል፡፡ የዘርፉ ምሁራን የሚመክሩት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ጥናት ላይ ተመስርቶ በእያንዳንዱ ምርትና አገልግሎት ላይ ያለው የፍላጎትና ምርት የሚገኝበትን ደረጃ ማወቅ ፣ ክፍተት ያለባቸውን ዘርፎች መለየት እና ክፍቱቱን መሙላት የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረት ቢያደርግ ውጤታማ መሆን ይችላል፡፡
ሀገራችን በምትከተለዉ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ፓሊሲ መሰረት ተገቢውን አሰራር ተከትሎ የንግድ ስርአቱን ግልጽ፣ ተድራሽና ውድድር የሰፈነበት ለማድረግ፣ የሸማቾችን ጤንነትና ደህንነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ፣ ሸማቾች ለከፈሉት ዋጋ ተመጣጣኝ የሆኑ ምርቶች ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ የማመቻቸት እንዲሁም ሸማቹን ከሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎች የሚከላከልና ለነጻ ገበያ ውድድር አመቺነት ያለው ሥርዓት ለማስፍን የንግዱ ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
በሀገራችን እስካሁን ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በሚፈለገው ደረጃ ባለመስፈኑ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር የምርቶች ዋጋ መናር ውድድርን በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ ከግብይት ሥርዓት አንፃር የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ ህግን ተከትለው በመስራት የሚገባቸውን ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ ነጋዴዎች እንዳሉ ሁሉ ሰበብ እየፈለጉ ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የሚዳክሩም አሉ፡፡
በተፈጠረው ሀገራዊ አለመረጋጋትና የፀጥታ ችግር ፤ የወጪ ምንዛሬ መጨመር ምክንያት እና በዓለም ላይ በድንገት በተከሰተው የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽን መከሰትን ምክንያት በማድረግ በምርቶች ላይ የተጋነነ ዋጋ መጨመር እየተለመደ መጥቷል፡፡
በያዝነው ዓመት አንዳንድ ነጋዴዎች ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር ከላይ የተጠቀሱትን ምክንያቶችን በመጠቀም ምርቶች ላይ ዋጋ ለመጨመር ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ይህ የዋጋ ጭማሪ ከላይ የጠቀስናቸው ምክንያቶች ብቻ የፈጠረው ተፅዕኖ ሳይሆን አጋጣሚውን እንደ ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም የተደረገ ሙከራ ነው፡፡
ስለሆነም መንግስት በሸማቾች ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎችን ለመቅረፍ እና በውድድር ላይ የተመሰረተ የግብይት ስርዓት ለመዘርጋት ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ የተለያዩ አሰራሮችን ዘርግቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
መንግስት በድጎማ የሚያቀርባቸውን መሰረታዊ ሸቀጦች ከራሱ ምንጭ የዉጪ ምንዛሬ በመመደብ እና የውጪ ምንዛሬ ባላቸው ባለሃብቶች (ዳያስፖራ አካውንትና የፍራንኮ ቫሉታ) ከታክስና ከግብር ነጻ ሆኖ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገባ እያደረገ ይገኛል።
የንግድ ዕቃዎች ዋጋ በመናሩ እንደሀገር የተፈጠረዉን የኑሮ ዉድነት ለመቀነስ ለንግዱ ማህበረሰብ በተለይም በ2013 በጀት ዓመት የመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት ከቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲገቡ የተፈቀዱ 5 የምግብ ሸቀጦች የምግብ ዘይት 416,354,906 ሊትር፤ ስኳር 4,479,422.8 ኩንታል፤ ሩዝ 9,238,775 ኩንታል፤ ስንዴ 265,750 ኩንታል፤ ዱቄት 11,400 ኩንታል የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖችን በማስተሳሰር በሁሉም ክልሎች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ የተደረገ ሲሆን የዉጭ ሀገር የምግብ ዘይት በማስቀረት በሀገር ዉስጥ አምራች ኢንዱስትሪ ለመተካት በተደረገ ጥራት ሁለት ፋብሪካዎች ማምረት ጀምረዋል፡፡
የሃገር ዉስጥ ምግብና ምግብ ነክ አምራች ኢንዱስትዎች ምርታቸውን ከፍላጎት እድገቱ ጋር እንዲያሳድጉ ድጋፍ የማድረጉና ያመረቱትን ምርት በተለይም የጅምላ ንግድን ከንግድ ሰንሰለቱ በማስወጣትና የግብይት ሂደቱን በማሳጠር አቅራቢዎች ለተመረጡ ቸርቻሪ ነጋዴዎችና ሸማቾች ማህበራት ዩኒየኖች እንዲያቀርቡ ማስቻል እንዲሁም አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የማገበያየት ትስስሮችም በተከታታይ እንዲያቀርቡ በማድረግ ህብረተሰቡ ትስስር ከተፈጠረለት አቅራቢዎች ኮታውን መጠየቅ የሚያስችለው አሰራር ተዘርግቶለታል፡፡
ከእነዚህም መካከል የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን በገበያ መረጃ ዳይሬክቶሬት ዕለታዊ የገበያ መረጃ የምርቶች ዋጋ ክትትል ያደርጋል፡፡ በዚህም መሰረት በምርቶች ላይ በተደረገ የዋጋ ዳሰሳ የብረታ ብረት ምርት፣ በአንዳንድ የግብርና ምርቶች ከሐምሌ ወር አሁን ላይ መጠነኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በተለይም ቀይና ነጭ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ካሮት፣ ፎሶልያ፣ ቃሪያ እና ጥቅል ጎመን ፤የአግሮ ኢንዱስትሪ ውጤቶች/ ፓስታ፣ መኮሮኒና ፍርኖ ዱቄት አልፎ አልፎ በሚከሰቱ ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች የተጋነነ ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል፡፡
መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ስርጭት በአግባቡ ካልተመራ ምርቶቹ ለብክነት የሚዳረጉ በመሆናቸው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሰረታዊ ሸቀጦች ስርጭት መመሪያ አዘጋጅቶ ለክልሎች ከዚህ ቀደም ያሰራጨ ሲሆን ክልሎችም እንደ ራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ መመሪያ አዘጋጅተው ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን አጠናክሮ ለማስኬድና ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ በንግድ እንቅስቃሴው ላይ ያለተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እና ምርትን በማከማቸት ሰውሰራሽ የገበያ እጥረት በሚፈጥሩ፤ የግብይት ሰንሰለቱን በማዛባት ምርት በገበያ ላይ እንዳይገኝ በሚያደርጉ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች እና ደላሎች ላይም የእርምት እርጃዎች የመውሰዱ ስራ በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ ለአብንት ያህል በንግድ ዕቃዎች ላይ ክትትል ቁጥጥር በማድረግ በ17 ጅምላ አካፋፋዮች እገዳ በ3 ፋብሪካዎች እና በ5 የመንግስት ልማት ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ገበያውን በማረጋገት ሕብረተሰቡን ከከፋ የኑሮ ውድነት ለመታደግ የምርት አቅርቦቱን ለማሻሻል ከተደረገው ጥረት ጎን ለጎን በየደረጃው በተዋቀረ ግብረ ሀይል በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር በህገ- ወጦች ላይ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ ለማሳያም በ72,171 የንግድ ድርጅቶች ላይ ማስጠንቀቂያ፣ በ46,523 የንግድ ድርጅቶች የታሸጉ፣ 104 ንግድ ፈቃዳቸው የታገደ፣ 320 ድርጅቶች የንግድ ፈቃድ የተሰረዘ፣ 1,223 የንግድ ተቋማት ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን 12,806,435 ብር በቅጣት ተሰብስቦ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የአምራች ኩባንያዎች ምርት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስና የውጭ ገበያ መቀዛቀዝ የነበረ ሲሆን የምርት አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ልዩ ልዩ ግብአቶችና ያለቀላቸው ምርቶች ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ ነጋዴውም ቢሆን ያመረተውን ሲሸጥ በሌላ በኩል መግዛቱ የማይቀር ነው፡፡ ለዚህም ነው “ሁሉም ሰው ሸማች ነው” የሚባለው፡፡ ሁሉም ሸማች በሆነበት ያልተገባ ዋጋ በምርቶች ላይ የሚጨምረው ማን ላይ ነው? የሸማቹን መብት አክብሮ በውድድር ተገቢ ትርፍ ለማግኘት የሚሰራ ነጋዴ ሀገር ውስጥ ይቅርና ባህር ተሻግሮ የገበያ ድርሻውን ማሳደግ ይችላል፡፡ ደንበኞችን በማቆየት ዘላቂ የሆነ ትርፍ ማግኘት የሚቻለው ምርታማነትን በማሻሻልና የግብይት ወጪዎችን በመቀነስ ተወዳዳሪ በመሆን እንጂ ምርትን በመደበቅ ወይም ያልተጠበቀ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ አይደለም እና አንድ ነገር ሻጭ ስንሆን ሸማች መሆናችንን እናስተውል፤ ህገወጥ አሰራርንም በጋራ እናክስም እንላለን፡፡