ሶማሊያ ከ27 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአየር ክልሏን በራሷ መቆጣጠር እና ማስተዳደር መጀመሯን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሞሀመድ አብዶላሂ (ፋርማጆ) አስታውቀዋል።
የምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር የአየር ክልል መቀመጫውን ኬንያ ናይሮቢ ባደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ቁጥጥር ስር ነበር ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ሲተዳደር የነበረው።
ፕሬዚዳንት ሞሀመድ አብዶላሂ፥ በሞቃዲሾ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ አስፈላጊው ቁሳቁስ የተሟላለትን የአየር ክልል መቆጣጠሪያ ቢሮ መርቀው ሲከፍቱ ነው ሶማሊያ የአየር ክልሏን በራሷ መቆጣጠር መጀመሯን ያበሰሩት።
“የአየር ክልላችን መልሰን በራሳችን አቅም መቆጣጠር መቻላችን በጣም ኩራት እንዲሰማን ያደርጋል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ቀኑንም ታሪካዊ ነው ብለዋል።
“ይህ በቀላሉ እና በእድል የመጣ አይደለም፤ የጠንካራ ስራ ውጤት እንጂ” ሲሉም ፕሬዚዳንት ሞሀመድ አብዶላሂ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱን የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና የሲቪል አቪዬሽን ሰራተኞች እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የሶማሊያ አውሮፕላን ማረፊያን በማስተዳደር ላይ የሚገኘውን ዓለም አቀፉን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት አመስግነዋል።
ሶማሊያ ለበርካታ ዓመታት ከአሸባሪው አልሸባብ ጋር ጦርነት ውስጥ የነበረች ሲሆን፥ በጦርነቱም በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሞተው በሚሊየን የሚቆጡ ዜጎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
ምንጭ፦(ኤፍ.ቢ.ሲ) africa.cgtn.com
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ