ማክሰኞ 27 ማርች 2018

ሰበር­_ዜና: ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ

ለቀናት ስብሰባውን ሲያካሂድ የቆየው የኢህአዴግ ምክር ቤት ዶክተር አብይ አህመድን የግንባሩ ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከግንባሩ ሊቀመንበርነት ለመነሳት ያስገቡትን መልቀቂያ መቀበሉን ተከትሎ ነው ምክር ቤቱ ምርጫ በማካሄድ ተተኪ የመረጠው። ምክር ቤቱ አቶ ደመቀ መኮንን የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው እንዲቀጥሉም ወስኗል።
                                                      ዶክተር አብይ አህመድ ማን ናቸው?

የትውልድ ስፍራ፦ ጅማ ዞን
የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በትራንፎርሜሽናል ሊደርሺፕ እና ቼንጅ፣ ማስተርስ ኢን ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እና በክሪፕቶ ግራፊ እንዲሁም የዶክትሬት ትምህርታቸውን በ“ፒስ ኤንድ ሴክዩሪቲ” አግኝተዋል።
የስራ ልምድ፦ በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ እስከ ሌፍተናንት ኮሎኔል ድረስ በተለያዩ ስፍራዎች ሲያገለግሉ ቆይተዋል፣ የፌደራል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የልህቀት ማእከል ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ውስጥም በምክትል ዳይሬክተርነት አገልግለዋል። በተጨማሪም የኢፌዴሪ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመሆኑ አገልግለዋል።
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ሃላፊ በመሆን ሰርተዋል።
ዶክተር አብይ አህመድ የኢህአዴግ አባል ድርጅት የሆነው ኦህዴድ ሊቀመንበር ናቸው።

(ኤፍ.ቢ.ሲ)

ረቡዕ 14 ማርች 2018

ከ4 ወራት በፊት ባለቤቱ በሞት የተለየበት ታማኝ ውሻ እስከአሁን ድረስ ከሆስፒታሉ በራፍ አልተንቀሳቀሰም

ከ4 ወራት በፊት ባለቤቱ በህመም ምክንያት በሞት የተለየበት ታማኝ ውሻ እስከአሁን ድረስ ከሆስፒታሉ በራፍ ባለ መንቀሳቀሱ የአለም መገናኛ ብዙሃን መወያያ ርእስ ሆነዋል።
የውሻው ባለቤት በጠና በመታመሙ ምክንያት ነበር ከሚኖርበት አከባቢ ወደ ብራዚል ሳኦ ፓሎ ሆስፒታል በአንቡላንስ የተወሰደው።
በዚህም ውሻው ይህ ሲያውቅ የአንቡላንሱን መንገድ በሩጫ ተከትሎ ሆስፒታሉ ድረስ መምጣቱ ሰራተኞች ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ የ59 አመት እድሜ የውሻው ባለቤት ህመሙ ከባድ ስለነበር የህክምና እርዳታ ሲያገኝበት ከነበረ ሆስፒታል ሳይወጣ ከአራት ወራት በፊት ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
ውሻው ግን ይህን አላምን በማለቱ ለባለቤቱ ጤና እየተመኘ እስከአሁን ድረስ ከሆስፒታሉ በራፍ ሳይንቀሳቀስ ባለቤቱ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ነው ተብሏል።

 ምንጭ፦www.odditycentral.com(ኤፍ.ቢ.ሲ)

ለሴት ልጃቸው የወንድ ስም የሰጡት ወላጆች ፍርድ ቤት ቀረቡ

ቤተሰቦች ስም ለማውጣት ብዙ ክርክሮች ያደርጋሉ ያለው ሚረር በፈረንሳይ ግን ከዚህ በተለየ ለሴት ልጃቸው የወንድ ስም በማውጣታቸው ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተነግሯል።
ለህፃኗ ልጅ ቤተሰቦቿ “ሊያም” የሚል ስም ቢያወጡላትም ፍርድ ቤቱ ለሴት ልጅ የሚሆን ስም አይደለም ብሎ ማገዱ ነው የተነገረው።
 የልጅቱ ስም የህፃናትን ፍላጎት የሚፃረር እና በማህበራዊ ግንኙነት ላይ ትፅዕኖ ሊያሳድር የሚችል በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ስሙን ሊያግደው እንደሚገባ አቃቤ ህጎች ተናግረዋል።
በተጨማሪም ስሙ ፆታዊ የሆኑ ብዠታዎችን ይፈጥራል ተብሏል።
ጉዳዩን የሚከታተለው ፍርድ ቤት የህፃኗ ቤተሰቦች አዲስ ስም እንዲያወጡ ማዘዙም ተገልጿል። 
ሆኖም የህፃኗ ቤተሰቦች ልጃቸው ባውጡላት ስም እንድትጠራ እንደሚፈልጉና ለዚህም የህግ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የተናገሩ ሲሆን፥ የህፃኗን ጥምቀት( baptism) ማራዘማቸው ታውቋል።
በልጃቸው ስም ምክንያት ፍርድ ቤት የቆሙት ወላጆች ጉዳይ ለልጆች ስም ማውጣት ላይ ጥብቅ ስርዓት አላት በምትባለው ፈረንሳይ ያልተለመደ መሆኑ ተነግሯል።
ከዚህ በፊት በፈረንሳይ ኑታላ፣ ስትሮዎበሪ እና ማንሃታ የተሰኙ ስሞች ለልጆች ማውጣት መከልከሉ ይታወሳል።
ምንጭ፦ ሚረር(ኤፍ.ቢ.ሲ)

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰንን ከኃላፊነት አነሱ

 የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰንን ከኃላፊነት አነሱ። በሬክስ ቲለርሰን ቦታም የሲ አይ ኤ ዳይሬክተር ማይክ ፔምፖንን ተክተዋል ነው የተባለው። 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰንን በትዊተር ገፃቸው ያመሰገኑት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፔምፖ መልካም ስራዎችን ይሰራሉ ሲሉ ምኞታቸውን ገልፀዋል።
የኤክሶንሞቢል ኩባንያ ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበሩት ሬክስ ቲለርሰን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ከአንድ ዓመት በፊት ነበር።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሆኑት የማይክ ፔምፖ የሲ.አይ.ኤ ዳይሬክተርነት ስፍራ ላይም የመጀመሪያዋ ሴት የሆኑትን ጊና ሀስፔልን በእጩነት አቅርበዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ (ኤፍ.ቢ.ሲ)

ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ ስቴፈን ሀውኪንግ ከዚህ ዓለም በሞት ተለ

የዓለማችን ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ ስቴፈን ሀውኪንግ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ቤተሰቦቻቸው አስታወቁ።  እንደ ቤተሰቦቹ ገለፃ፥ ስቴፈን ሀውኪንግ ዛሬ ማለዳ ላይ በቤታቸው እያሉ አርፈዋል።“በጣም የምንወደው አባታችን ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶናል” ሲሉም የስቴፈን ሀውኪንግ ልጆች ተናግረዋል። የፌዚክስ ሊቅ የሆኑት እንግሊዛዊው ስቴፈን ሀውኪንግ “ብላክ ሆልስ” እና “ሪላቲቪቲ” በሚባሉ የፊዚክስ ስራዎቻቸው የሚታወቁ ሲሆን፥ “ብሪፍ ሂስትሪ ኦፍ ታይም” የሚለውን ጨምሮ በርከት ያሉ የሳይንስ መጻህፍቶችንም ጽፈዋል።
ስቴፈን የ22 ዓመት ወጣት እያሉ ባጋጠማቸው የነርቭ ህመም ያለ ድጋፍ ሰጪ መሳሪያ መናገርም ሆነ መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቆይተዋል።
ስቴፈን ሀውኪንክ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥር 8 1942 ላይ ነበር በእንግሊዟ ኦክስፎርድ የተወለዱት።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1959 በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በተፈጥሮ ሳይንስ ያጠኑት ሀውኪንግ፥ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ከካንብሪጅ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል;። 
በፈረንጆቹ 1963 “ሞቶር ኔውሮን” በተባለ የነርቭ በሽታ የተጠቁት ስቴፈን በወቅቱም ከዚህ በኋላ በህይወት የሚኖሩት 2 ዓመት ብቻ ነው ተብለው ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1988 ያሳተሙት “ብሪፍ ሂስትሪ ኦፍ ታይም” የሚለው መጽሃፋቸውም በዓለም ዙሪያ በ10 ሚሊየን ኮፒ መሸጡ ይታወሳል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ (ኤፍ.ቢ.ሲ)