የዛሬ 120 ዓመት የካቲት 23 ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት ተጀምሮ ለሰዓታት በተካሄደው ጦርነት ኢትዮጵያውን የህይወት መስዋትነት ከፍለው አድዋ ላይ ፋሺስት ኢጣሊያን ድልነስተው አንገቱን ሲያስደፋ፣ የኢትዮጵያ ዝና በዓለም እንዲናኝና አገሪቷም ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ማድረጋቸው የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ፡፡
አድዋ ከኢትዮጵያ አልፎ የጥቁር ሕዝቦችን ነፃነትና ክብርን ያረጋገጠ፣ የቅኝ ገዢዎችን የመስፋፋት ህልም የገታ፣ በቅኝ ግዛት ሥር ለወደቁና ወረራ ለሚቃጣባቸው አገሮች ትልቅ ምሳሌ የሆነ የኢትዮጵያንና የአፍሪካውያን የድሎች ሁሉ ድል መሆኑ የተመሰከረለት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ነፃነቷ እንዲጠበቅ ያደረጉ ጀግኖችን በክብር ለመዘከርና ትውልዱም ቃል ኪዳኑን ለማደስ የካቲት 23 ቀን በየዓመቱ ይከበራል፡፡
የአደዋ ጦርነት መነሻ ሰበቡ ጣሊያኖች ኢትዮጵያን በቅኝ አገዛዝ ቁጥጥር ውስጥ ለማድረግ ከኢትዮጵያው ንጉስ ነገስት አጤ ሚኒሊክ ጋር ባደረጉት የውጫሌ ውል አንቀፅ 17 ላይ ያስቀመጡት አቋም ነበር፡፡ በአማርኛ የተፃፈው 17ኛው አንቀፅ የሚለው <<የኢትዮጵያ መንግስት ከሌሎች መንግስታት ጋር ለሚያደርገው ጉዳይ በኢጣሊያ አማካይነት ሊያደርገው እንደሚችል…>>የሚል እንደምታ ያለው ሲሆን፣ የኢጣሊያ መንግስት በሁለት ቋንቋ በተለያዩ ዘርፎች ለራሱ በሚመቸው መንገድ ያስቀመጠው ነበር፡፡ ይህንን የኢጣሊያ መንግስት ተንኮል የተረዱት አጤ ሚኒሊክ ውሉ እንዲስተካከል ይጠይቃሉ፡፡ ጥያቄያቸውም በአጭሩ እንዲህ የሚል ነበር፡፡ <<በንግሴ ምክንያት ወዳጆች ለሆኑት የአውሮፓ መንግሥቶች ከነጉስ ነገሥት ዙፋን ላይ መውጣቴን ባስታውቃቸው በመጣልኝ ምላሽ
ውስጥ መንግስሥቴን የሚያንኮስስ ነገር አገኘሁበት፡፡ የዚህ መሰረትም የሚገኘው የውጫሌ ውል ላይ በሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም በተደረገው ውል 17ኛው አንቀፅ ውስጥ ነው፡፡ ይህንን አንቀፅ ደህና አድርገን ከተመለከትነው በኋላ ፣ የአማርኛው ምንጭና የኢጣሊያንኛው ትርጉም የማይገጣጠሙ መሆናቸውን አረጋግጥን፡፡ >>እኔ ለኢጣሊያ ስለወዳጅነት ብዬ ይኸን ውል ስገባ ምስጢራችን ተጠብቆ እንዲኖር ጉዳያችንም እንዳይበላሽ በማለት በአውሮፓ ለሚሆኑ የንግድ ጉዳዮቻችን በወዳጅነት በኢጣሊያ ንጉስ መንግስት ረዳትነት ሊደረጉ የሚችሉ መሆኑን ተናገርኩ እንጂ ለዚህ የሚያስገድደኝ ውል አልገባሁም፡፡
ግርማዊ ንጉሥ አንድ የሌላ መንግስት ያልሆነ መንግሥት ረዳትነት በወዳጅነት ብቻ እንደሚፈልገው ይገባዎታል፡፡ ከዚህ በቀር የውሉን 19ኛ አንቀፅ በሁለቱም ቋንቋዎች የቃሉ ሃሳብ የተስማማ እንደሆነ ብቻ ውልነታቸው የሚፀና መሆኑን የሚያመለክተውን ልብ አድርገው ይመልከቱት…አሁን እርስዎ ለወዳጀዎ ክብር ብለው በ17ኛው አንቀፅ የተደረገውን ስህተት እንዲቃና እንዲያስደርጉትና ይህን አንቀፅ ላስታወቋቸው መንግስታቶች ስህተቱን እንዲገልጹላቸው እመኛለሁ፡፡
ይህ የአጤ ሚኒሊክ ደብዳቤ የሚያሳየው ብልህነታቸውን ነው፡፡ ጣሊያን በ17ኛው አንቀፅ እርሳቸውን ያሳሳቱ ቢመስላቸውም እርሳቸው ግን በ19ኛው አንቀፅ ላይ ያለውን << በሁሉቱም ቋንቋዎች የቃሉ ሃሳብ የተስማማ እንደሆነ ብቻ ውሉ የሚፀና መሆኑን >>በመጥቀስ የጣሊያንን ሻጥር ውድቅ አድርገውታል፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ ዲፕሎማሲያዊም በሆነ መንገድ መጀመሪያ ከራሱ ከጣሊያን መንግሥት ጋር ለመስማማት ሙከራ በማድረግ ነው ፡፡
የጣሊያን መንግስት የንጉስ አጤ ምንሊክን ጥያቄ ውድቅ አደረገ፡፡ ለድርድሩ የተላከው አንቶኔሊም << ውጫሌ የተዋዋልንበት ወረቀት በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተጣፈው ይታይልኝ>> ብሎ አመለከተ ፡፡ እቴጌ ጣይቱም << እኛ የምናውቀው በአማርኛ የተጣፈውን ነው እንጂ የፈረንጅ ቋንቋ አናውቅም፡፡አንተ ግን የእኛን ቋንቋ ታውቃለህና በአማርኛ የተጣፈውን እየው>> አሉት ፡፡ ከዚህ በኋላ ኮንት አንቶኔሊ ተናዶ ያን ትናንት የተፃፈውን ወረቀት ቀዳዶ ጥሎ ውሎን የኢጣሊያ መንግሥት በጦር ኃይል እንደሚያስከብር ተናገረ፡፡ ይህን የሰሙት እቴጌ ጣይቱም ስቀው <<የዛሬ ሳምንት አድርገው ፡፡ በዚህ የሚደነግጥልህ የለም፡፡ሂድ የፎከርክበትን አድርግ እኛም የመጣውን እናነሳዋለን፡፡ እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰው በዚህ የሌለ አይምሰልህ የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ አገሩ መሞት
ጌጡ እንጂ ሞት አይባልም፡፡ አሁንም ሂድ አይምሽብህ ፣ የፎከርክበትን በፈቀደህ ጊዜ አድርገው፡፡ እኛም ከዚህ እንቆይሃለን፡፡>> አሉት፡፡
የጦር ስትራቴጂ ቀያሽና ልበ ሙሉ የሆኑት እቴጌ ጣይቱ አንቶኔሊ የውሉን ማሻሻያ ቀዳዶ በጣለው ጊዜ <<… እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፡፡ ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከመቀበል ጦርነት እመርጣለሁ >>አሉ፡፡ ከዚህ በኋላ በጉዳዩ የተናደዱት አጤ ሚኒሊክ የውጫሌውን ውል በተዋወሉ በ4ኛው ዓመት ለኤሮፓ ኃያላን ይህ የአጤ ሚንሊክ ደብዳቤ የሚያሳየው ብልህነታቸውን ነው፡፡ ጣሊያን በ17ኛው አንቀፅ እርሳቸውን ያሳሳቱ ቢመስላቸውም እርሳቸው ግን በ19ኛው አንቀፅ ላይ ያለውን << በሁለቱም ቋንቋዎች የቃሉ ሃሳብ የተስማማ እንደሆነ ብቻ ውሉ የሚፀና መሆኑን>> በመጠቆም የጣሊያንን ሻጥር ውድቅ አድርገውታል፡፡
መንግስታት ሁሉ አድራሻው እየተለዋወጠ ቃሉ አንድ አይነት የሆነውን የውጫሌውን ውል ያፈራረሙበትን ደብዳቤ ፃፉ ፡፡ የአጤ ምንሊክ ደብዳቤ የደረሳቸው ነገስታትና መንግስታት በሁለት ጉራ ተከፍለው ነበር ፡፡ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ልታጠፋት ትችላለች የሚል አመለካከት የነበራቸው ሁሉ ነበሩ፡፡
አንዳንዱቹ ኢትዮጵያን ጥገኝነት ተቀብላ በውጫሌው ውል እንድትረጋ መከሩ፡፡ የእንግሊዟ ንግስት ቪክቶሪያ ለሚኒሊክ በፃፉት ደብዳቤ በኢጣሊያ ጥገኝነት ስር እንዲቆዩና ለኢትዮጵያም የሚሻለው ዘዴ ይኸው መሆኑን ገለጡላቸው ፡፡ የጀርመን ንጉስ ነገስት ተመሳሳይ ደብዳቤ ፃፉ ፡፡ አጤ ሚኒሊክ ግን ጉዳዩን እንደገና ከመረመሩ በኃላ ለሁለት ነገስታት እንደገና ደብዳቤ ፃፉላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ ኢጣሊያኑች ሁሉ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ አዘዙ ፡፡ ለጣሊያን መንግስት << ወደፊት ማንኛውም የኢጣሊያ ሰው ወደ ሀገሪ እንዳይመጣብኝ ይሁን >> ብለው በደብዳቤ አሳወቁ ፡፡ የአጤ ሚኒሊክ ውሳኔ ያስደነገጠው የኢጣሊያ መንግስት ስለ ውጫሌ ውል እንዲነጋገር ዶክተር ትራቨርሲን ሁለት ሚሊዩን ጥይት ገፀ በረከት አስይዘው እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ላከው፡፡ አጤ ሚኒሊክም ከዶክተር ትራቨርሲን ጋር በተገናኙ ግዜ << እኔ በማናቸውም ቢሆን ከኢጣሊያ መንግስት ጋር የጀመርኩት ወዳጅነት ለመተው አሳብ አልነበረኝም፡፡ እናንተ ግን አሳባችሁ ሁሉ ለጠብ እንጂ ለፍቅር አለመሆኑን ሥራችሁ ይመሰክራል፡፡ >> ብለው እንደገና ለድርድር ቢዘጋጁም የኢጣሊያን መንግስት ግን በድርድር ሰበብ ጦሩን ማደራጀት ጀምሩና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን መሳፍንቱች
በገንዘብ በመደለል በምንሊክ ላይ እንዲያምፁ ጥረት በማድረግ፣ እንዲሆም በተለያዩ መንገዶች የምንሊክን መንግስት ለማዳከም ይሰራ ጀመር፡፡
የኢጣሊያን መንግስት ከምንሊክ ጋር የጀመረውን ድርድር ሳይጨርስ፣ በ1887 ዓ.ም በጀነራል ኦሬሮ የሚመራው የኢጣሊያ ጦር አድዋ ገብቶ አገሩን ያዘ፡፡ አድግራትና መቀሌ መጋቢት 16 ቀን ተያዙ፡፡ አክሱም ገብቶ ለህዝቡ ልብስና ማባበያ መበስጠት << ከሚንሊክ አገዛዝ ነፃ ላወጣትችሁ ነው >> እያለ ይሰብክ ነበር፡፡ የጣሊያን ጦር ሀገር እየወረረና እየዘረፈ ብዙ ደም ያፈስ ነበር፡፡ በዚህ የተበሳጩት አጤ ምንሊክ ትግስታቸው በማለቁ ከጣሊያን ጋር ለመፋለም ወስነው የሚከተለውን አዋጅ አወጁ ፡፡<< አሁን ግን በእግዚያብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፊ አልሰጥም ፡፡ያሀገሬ ሰው፣ ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሀይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም ዘመቻዩ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡>>
የሀይል አሰላለፍን በተመለከተ ጳውሎስ ኞኞ በፃፈውና አጤ ምንሊክ በተሰኘው መፃፍ ላይ ወደ አድዋ የዘመተው የኢትዩጵያ ጦር ብዛቱ በትክክል አይታወቀም፡፡ ብዙ ታሪክ ፃፊዎችም የፃፉት የተለያ ቁጥር ነው፡፡ ቱኪ የተባለው ፀሐፊ የኢትዪጵያ ወታደር ከ70.000 እስከ 80.000 ይደርሳል ይልና ከነዚህም ውስጥ ጠመንጃ ያላቸው 25.000 ሰዎች ናቸው ብሏል፡፡ አንቶኔሊ ደግሞ ከ110.000 ሺህ እስከ 120.000 ሺህ ነው ሲል ፣ ባራቲየር እንደፃፈው ደግሞ ከ75.000 እስከ 80.000 ይደርሳል ብሏል፡፡ ኢልግ 150.000 ነው ሲል ዌልቤ ደግሞ በሚኒሊክ ጥሪ የተሰበሰበው 200.000 ሺህ ነው ይላል << ይህ ሰራዊት በሙሉ ጦርነቱ ቦታ አልደረሰም፡፡ ሰራዊቱ ገና በጉዙ ላይ እንዳለ ጦርነቱ አለቀ ይላል፡፡
ዌልዴ የተባለው ፀሐፊ ደግሞ 120.000 ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ተካፍለዋል ሲል የምንሊክ መድፍ አስተኳሽ የነበረው ፈረንሳይዊ ካፒቲን ክሎቼቴ 150.000 እንሆነ ሲል ፅፋል ፡፡ በርከት ያሉ ፀሐፊዎች የተስማሙበት የዘማቹ ቁጥር ግን አጤ ሚንሊክ 30.000 እግረኛ እና 12.000 ፈረሰኛ ፣ እቴጌ ጣይቱ 3000 እግረኛና 6000 ፈረሰኛ ፣ራስ መኩንን 15.000 እግረኛና ራስ መንገሻ ዮሐንስ 12.000 እግረኛና ፣ ራስ ሚካኤል 6000 እግረኛና 10.000 ፈረሰኛ ፣ ራስ አሉላ 3000 እግረኛ፣ አዛዥ ወለደጣዲቅ 3000 እግረኛ ፣ደጃች ተሰማ ናደው 4.000 ራስ ዳርጌ ፣ ግራዝማች በንቲና ቀኝ አዝማች ሞንን 20.000 እግረኛ ወታደሮች አሰልፈው ነበር፡፡>> በኢጣሊያ በኩል የቅኝ ግዛተ ወታደር ሳይጨምር 17.000 ኢጣሊያውያን ከ56 መድፎች ጋር ተሰልፈው ነበር፡፡ በኢጣሊያ በኩል የተሰለፈው ወታደር እጅግ ዘመናዊ የሆነና የሰለጠነ ወታደር ነበር፡፡
በምንሊክ በኩል የመድፎች ብዛት 42 ሲሆን፣ እነዚህም የኢጣሊያን ዘመናዊ የተራራ መድፍ የማይወዳዱሩ ነበሩ፡፡ በዚህ ከፍተኛ ጦርነት 7ሺ 560 ኢጣሊያውያንና 7ሺ100 ጥቂት ወታደሮች /ለጣሊያን የተሰለፉ/ ሲገደሉ 954 ኢጣሊያኖች ጠፍተዋል፡፡ 470 ኢጣሊያውያንና 958 ጥቁር ወታደሮች በጠቅላላው 1428 የጠላት ወታደሮች ሲቆስሉ፣ 11.000 ጠመንጃና የነበሯቸው መድፎች በሙሉ ተማረኩ፡፡ በኢትዮጵውያን በኩል 7.000 ሰዎች ሲሞቱ፣ 10.000 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ፡፡
የተማረከ ወታደርና መሳሪያ ግን አልነበረም ፡፡ ይህ በብዙው ዓለም ያልተለመደ ታላቅ ድል በተለይ ለጥቁር ሕዝቦች የብርሃን ችቦ የፈነጠቀ ድል ሆኖ በታሪክ ተመዘገበ፡፡
ሚኒሊክ ድል አድራጊ ወታደራቸውን እየመሩ በግንቦት 3 ቀን 1888 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቡ፡፡ በአፍሪካ የጦርነት ታሪክ ውስጥ ሁለት የተከበሩና የተደነቁ ጦርነቶች አሉ፡፡ አንደኛው ከ2000 ዓመታት በፊት ሀኒባል ኤሮፓውያንን ድል ያደረገበት ጦርነት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከ2000 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ በአድዋ ጦርነት ኤሮፖውያንን ድል የመቱበት ጦርነት ነው፡፡ ይህንንም ብዙ ታሪክ ፀሐፊዎች ፅፈውት ይገኛል፡፡
ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካውያን በታላቁ የአድዋ ድል እንኮራለን፡፡ በአባቶቻችን የፀና ድልም እንፅናናለን፡፡ ነገር ግን በኩራትና ታሪክ በመዘከር ብቻ ደግሞ አንቆምም፡፡ ይልቁንም እንደ አዲስ ትውልድ ከፊታችን ስለተደቀነው ድህነትና ኋላቀርነትን የማሸነፍ ትግል እንዘምራለን በአባቶቻችን ብርቱ ወኔ ጭምር እየታገዝንም ለሌላ አኩሪ ድል እንተጋለን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ