እሑድ 24 ዲሴምበር 2017

የንግድ ፍቃድ እድሳት ያደረጉ ነጋዴዎች ከሃምሳ በመቶ በታች መሆኑ ተገለጸ

 የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የ2010 በጀት ዓመት የንግድ ሥራ ፍቃድ ዕድሳት ያደረጉ ነጋዴዎች ከሃምሳ በመቶ በታች መሆናቸውን አስታወቀ፡፡የንግዱ ማህበረሰብ እስከ ታኀሣሥ 30 ያለ ቅጣት እንዲያሳድስ ጥሪ አቀረበ። 
የቢሮው የንግድ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ተገኝ ትናንት እንዳስታወቁት፣ቢሮው ከሐምሌ አንድ እስከ ታኀሣሥ30/2010 ድረስ ለ276ሺ 688 ነጋዴዎች የፍቃድ ዕድሳት ለማድረግ አቅዶ እስከ ታኀሣሥ 12/2010ዓ.ም ዕድሳት ያደረገው ለ122ሺ752 ነጋዴዎች ብቻ ነው፡፡ይህም የዕቅዱ 47 በመቶ ነው።
እንደ አቶ ብርሃኑ ማብራሪያ ነጋዴዎች የፍቃድ ዕድሳት እንዳያደርጉ አንዱ ምክንያት ከቀን ገቢ ግመታ ጋር ተያይዞ ቅሬታ በማስገባታቸው ነው፡፡ ይሄም ቤት ለቤት ቅስቀሳ በሚደረግበት ወቅት ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት ቅሬታ ያስገቡ ነጋዴዎች ፍቃድ እንዲያድሱ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ቅሬታ ያላቸው የንግዱ ማህበረሰብ ቅሬታችን አልታየም በሚል በክሪላንስ እጦት ፍቃዳቸውን ሳያድሱ ለቅጣት እንዳይዳረጉ ከገቢዎችና ጉምሩክ ጋር በመነጋገር ክሪላንሱ እንዲሰጣቸው አቅጣጫ መቀመጡን አብራርተዋል፡፡ ክሪላንስ ወስደው ፍቃዳቸውን ካደሱ በኋላ በየትኛውም ጊዜ ቅሬታቸው ሊታይ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
አብዛኛው ነጋዴ በታኀሣሥ ወር ንግድ ፍቃዱን የማደስ ባህል እንዳለው የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በቀረው ጊዜ ውስጥ ክሪላንስ ወስደው ማደስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ነጋዴውን ለማስተናገድ ሠራተኞች ከሥራ ቀን በተጨማሪ ቅዳሜ እና እሁድን ጭምር እንደሚያገለግሉ አስታውቀዋል፡፡
‹‹የንግድ አዋጁ ነጋዴው ማህበረሰብ እስከ ታኀሣሥ 30 ብቻ ፍቃዱን እንዲያድስ ነው የሚያዘው ›› ያሉት አቶ ብርሃኑ የጥር ወር ከገባ በኋላ ግን ፍቃድ ለማደስ 2ሺ 500 ብር ቅጣት እንዳለውና ይሄም ጊዜው በጨመረ ቁጥር እያደገ የሚሄድ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡
 አዲስ ዘመን (ሰብስቤ ኃይሉ)

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ