እሑድ 24 ዲሴምበር 2017

የቂሊንጦ መድኃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ 75 በመቶ ተጠናቋል

የቂሊንጦ መድኃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ 75 በመቶ መጠናቀቁን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለፀ።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን በስፋት ለማሳተፍ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባች መሆኑ ይታወቃል። 
ከነዚሁ ፓርኮች መካከል በ270 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ከ2009 ዓ.ም የካቲት ወር ጀምሮ በቻይናው ቲ ሴ ጁ ሲቪል እንጂነሪግ ግሩፕ እየተገነባ ያለው የቂሊንጦ መድኃኒት ማምረቻ ኢንዱስተሪ ፓርክ አንዱ ነው። 
ከ5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቀው ይህ ፓርክ ከዓለም ባንክ በብድር በተገኘ ገንዘብ በመገንባት ላይ ሲሆን በመጭዎቹ ሶስት ወራት ግንባታው እንደሚጠናቀቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል። 
በኮርፖሬሽኑ የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፕሮጀክት ኢንጅነር የጌታሁን አገኘሁ ለኢዜአ እንዳሉት የግንባታው ዋና ዋና የሚባሉ ሥራዎች ተጠናቀዋል።
ግንባታውን በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ የታቀደ ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት የፓርኩ ግንባታ 75 በመቶ ተጠናቋል ብለዋል።
የስድስት ወኃ ጉድጓዶች ቁፋሮና 2 ትልልቅ የውሃ ማከማቻ ማማዎች ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በፓርኩ ውስጥ የሚካሄደው የመንገድ ግንባታና አቋርጦ የሚያልፈውን ወኃ ማሸገሪያ ሶስት ድልድዮች ሥራዎችም መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። 
ለመድኃኒት ማምረቻ ሼዶች ግንባታ ቦታውን ምቹ ለማድረግ የሚከናወኑ የአፈር ቆረጣና መሙላት ስራዎችም በአብዛኛው መጠናቀቃቸውን የተናገሩት አቶ የጌታሁን እየተገነባ ባለው መንገድ ግራ እና ቀኝ ጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎች ስራም 95 በመቶ መከናወኑን አንስተዋል። 
የፓርኩ የአስተዳደር ህንጻ ግንባታ እተየገባደደ መሆኑን የጠቀሱት ኢንጅነር የጌታሁን የፓርኩ አጥር፣ ፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መስመር፣ የኤሌክትሮኒክስና ቴሎኮም መስመር ዝርጋታ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል። 
ከዲዛይንና ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ምክንያት ሥራው በሚጠበቀው ፍጥነት እንዳልተጓዘ ነው የተናገሩት።
እንደ ፕሮጀክት ኢንጅነሩ ገለፃ ''በአጋጠሙ ችግሮች ምክንያት የባከነውን ጊዜ ለማካካስ ግንባታውን የሚያካሂደው ተቋራጭ ቀንና ማታ ከሁለት ሽፍት በላይ እየተሰራ ነው።'' 
የፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ 18 ኪሎ ሜትር የሚረዝም አስፋልት መንገድ፣ የውሃ አቅርቦት አገልግሎቶች፣ የሎጅስቲክ ሼዶች፣ የአረንጓዴ ቦታዎች፣ መጋዘኖች፣ መዝናኛ ማዕከላት፣ የቢዝነስ ማከላት፣ መኪና ማቆሚያ ቦታዎችን የመሳሰሉ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ይሆናል። 
ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ከሚያስፈልጋት መድኃኒት 80 በመቶ ያህሉን ከውጭ አገራት በከፍተኛ ውጭ ምንዛሬ የምታስገባ ሲሆን፥ የቂሊንጦ መድኃኒት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፍላጎቱን በአገር ውስጥ ምርት ከመሸፈን ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንደሚያስገኝ ይጠበቃል።
ምንጭ፦(ኤፍ ቢ ሲ) ኢዜአ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ