ረቡዕ 20 ዲሴምበር 2017

ጀርመናዊው የባንክ ሰራተኛ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሳንቲሞችን ለመቁጠር ስድስት ወራት አስፈልጎታል

 ብሬሜርቮርድ በተሰኘችው አነስተኛና ጥንታዊ ከተማ የሚኖሩ ቤተሰቦች አሁን በህይዎት ከሌለውና በአሸከርካሪነት ያገለግል ከነበረ የቀድሞ የቤተሰባቸው አባል 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የደች ፍራንክ (የቀድሞ የጀርመን ገንዘብ) በውርስ አግኝተዋል።
እነዚህ የቀድሞ የምዕራብ ጀርመን መገበያያ ገንዘቦች ደግሞ ባለ 1 እና ባለ 2 ደች ፍራንክ ናቸው።
ይህ ውርስ የተገኘው ስሙ ያልተጠቀሰው የቤተሰቡ አባል በአሽከርካሪነት በሚሰራበት ወቅት ለቤተሰቤ በሚል ከ30 አመታት በፊት እየቆጠበ ካስቀመጣቸው የሃገሪቱ የቀድሞ ሳንቲሞች ነው።
አንድ ሁለት እያለ የጀመረው ቁጠባ ተጠራቅሞ ከ30 አመታት በኋላ የገንዘቡ መጠን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የደች ፍራንክ ይደርሳል።
እነዚህን ፍራንኮች የወረሱት የቀድሞው አሽከርካሪ ቤተሰቦች ታዲያ ወደ ሃገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ በመሄድ እነዚህ ገንዘቦች ይመነዘሩላቸው ዘንድ ይጠይቃሉ።
ገንዘቦቹ 2 ነጥብ 5 ቶን ወይም 2 ሺህ 500 ኪሎ ግራም ይመዝኑ ነበር።
ባንኩም ገንዘቡን ለመቁጠር ማሽን መጠቀም ቢያስፈልገውም ገንዘቦቹ ከመቀመጥ ብዛት የተወሰነ የሻገቱና የተያያዙ በመሆናቸው ማሽን የመጠቀም አማራጩን ይሰርዛል።
ምክንያቱ ደግሞ በዚህ መልኩ የተጣበቁና የሻገቱት ገንዘቦች ማሽኑን ለጉዳት ይዳርጉታል የሚል ነበር።
በዚህ ሳቢያም በማዕከላዊ ባንኩ የሚሰራውና ወልፍጋንግ ኬሜሪት የተሰኘው ሰራተኛ እነዚህን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የቀድሞ የደች ፍራንኮች እንዲቆጥር ሃላፊነቱ ይሰጠዋል።
እርሱም እጅግ አሰልቺ የተባለውን ቆጠራ አንድ ብሎ በመጀመር ገንዘቦችን እየጠረገና እያስተካከለ ቆጥሮ ይጨርሳል።
ይህን ለማድረግ ግን ቀላል ጊዜ አላሳለፈም ፤ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን የደች ፍራንኮችን ቆጥሮ ለመጨረስ ስድስት ወራትና ተጨማሪ ቀናት አስፈልገውታል።
በእጁ ለመቁጠር ስድስት ወራትና የተወሰነ ቀን በጠየቀው ሃላፊነት ግን ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።
ይህ ሁሉ ሆኖ ግለሰቡ ከስድስት ወራት በላይ ገንዘቦቹን ለመቁጠር ጊዜ ቢወስድበትም የገንዘቡ ምንዛሪ ግን እጅግ ቀላል ነበር።
የቀድሞዎቹ መገበያያ ገንዘቦች አሁን ባለው ዋጋ 8 ሺህ ዩሮ ብቻ ተመንዝረዋል።
የአሽከርካሪው ቤተሰቦችም በመለስተኛ ተሽከርካሪ አስጭነው ባመጡት የቀድሞ ገንዘብ ምትክ፥ በኪስ የሚያዝ ዩሮን ይዘው ተመልሰዋል።
የሃገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ አሁን ላይ 12 ነጥብ 65 የቀድሞ የጀርመን መገበያያ ገንዘብ በግለሰቦች እጅ እንደሚገኝ ይገልጻል።
ባንኩም ግለሰቦቹ ፈቃደኛ ከሆኑ እነዚህን ገንዘቦች በዘመናዊው መገበያያ ገንዘብ ዩሮ ለመቀየር ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ