By besufkad zena@ DireTube
---------------------------------------
በባለፈው ጽሁፎቼ ላይ ትዳር በሁለት ሰዎች(በወንድ እና
በሴት) በጎ ፈቃድ የሚመሰረት ህጋዊና ማህበራዊ
ስምምነት እንደሆነ ጠቅሼ ነበር፡፡ሰዎች በትዳር ውስጥ
የሚኖሩት ተስማምተውና ተረዳድተው መኖር ሲችሉ ነው፡፡
ነገር ግን መስማማት ካቃታቸውና በመሀከላቸው
የሚኖረው ልዩነት እየሰፋ የሚመጣ ከሆነ ወደፍቺ
ያመራሉ፡፡ በምዕራባውያኑ አለም የሚፋቱ ሰዎች ቁጥር
በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል፡፡
----
በሀገራችንም ቢሆን እንደ ምዕራባውያኑ ባይሆንም
የተፋቺዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛ፡፡
በዛው በምዕራቡ አለም የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት
ፍቺ ሰዎችን ጭንቀት ውስጥ ከሚከቱ የህይወት
አጋጣሚዎች ሁሉ በአንደኝነት የተቀመጠ ነገር ነው፡፡
ግላዊነት በሚንጸባረቅበት የምእራቡ አለም ፍቺ እንደዚህ
አስጨናቂ ነገር ከሆነ ማህበራዊነት በሚንጸባረቅበት በእኛ
ባህል ፍቺ ምን ያክል ከባድ ተጽእኖ እንዳለው መገመት
አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ የእኛ መፋታት በዙሪያችን ያሉ ሰዎች
ላይ ሁሉ ከፍተኛ ተጽእኖ ይፈጥራል ስለዚህ በጣም
ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
------------
የፍቺ ደረጃዎች
ፍቺ በአንድ ለሊት የሚከናወን ነገር አይደለም፡፡ ቀስ በቀስ
ከአንድ ደረጃ ወደሌላ ደረጃ እየተሸጋገረ በስተመጨረሻ
ሰዎችን የሚያለያይ እና ቤተሰብን የሚያፈርስ ጉዳይ ነው፡፡
በትዳራችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ጥቃቅን የሚመስሉ
ችግሮች ወድያውኑ መፍትሄ እየሰጠናቸው ካልሄድን
ጥቃቅን ብለን ያሰብናቸው ችግሮች ጥርቅም ትልቅ
ችግር ከመሆን አልፎ ለፍቺ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
የፍቺን ደረጃዎች ከዚህ እንደሚከተለው እናያቸዋለን፡፡
-----
1. ሀይለስሜታዊ ፍቺ
ይህ ደረጃ የፍቺ የመጀመሪያ ደረጃ ሲሆን እዚህ ደረጃ
ላይ የደረሱ ባለትዳሮቹ አንድ ቤት ውስጥ የሚኖረው
አካላቸው ብቻ ነው፣ምንም አይነት የስሜት ቁርኝት
የላቸውም:: ከውጪ የሚመለከተው ሰው ብቻ ትዳር
ውስጥ እንዳሉ ይታየዋል፡፡
--------
2. ፍቺን ማጽደቅ
ይህ ደረጃ ተጋቢዎቹ ፍርድ ቤት ሄደው ትዳራቸውን
የሚያፈርሱበት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ከውጪ ሆኖ ሲመለከት
ለነበረ ሰውም የትዳር መፍረስ የሚታወጅበት ነው፡፡
--------
3. የንብረት ክፍፍል
ይህ ደረጃ ባለትዳሮቹ አብረው ሲኖሩ ያፈሩትን ሀብት
በሚደርሳቸው መሰረት የሚከፋፈሉበት ነው፡፡
----
4. የቤተሰብ ክፍፍል
ይህ ደረጃ ባለትዳሮቹ አብረው ሲኖሩ ልጅ ወልደው ከሆነ
የልጆቻቸውን እጣ ፋንታ የሚወስኑበት ነው፡፡
------------
5. ስነልቦናዊ ፍቺ
በዚህ ደረጃ ላይ ፍቺ ይጠናቀቅና የተፋቱት ባልና ሚስቶች
እንዴት ሆነው መኖር እንዳለባቸው የሚያስቡበት
እንዲሁም አዲሱ ህይወታቸውን ለመላመድ የሚጥሩበት
ነው፡፡
------
የፍቺ አሉታዊ ተጽእኖ
ፍቺ እጅግ በጣም ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ ያለው፣ ትልቅ
ማህበራዊ ተቋምን የሚያፈርስ እና በሀገር ላይ ከፍተኛ
ቀውስን የሚያስከትል ሂደት ነው፡፡ ከተለያዩ የጥናት
ውጤቶች ላይ ያገኘኋቸውን የፍቺ አሉታዊ ተጽዕኖዎች
ከዚህ እንደሚከተለው አቀርብላችኋላው፡፡
----
1. በልጆች ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ
የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ወላጆቻቸው በፍቺ
የተለያዩባቸው ልጆች ላይ ከፍተኛ ድብርት፣ የትምህርት
ውጤት መቀነስ፣ ከሰዎች ጋር መስማማት አለመቻል ፣
በሚያድጉበት ወቅትም ለትዳር አሉታዊ አመለካከት
ማሳየት….ወዘተ ይታይባቸዋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት
ፍቺ ከሴት ልጅ ይልቅ ወንድ ልጅ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ
ያሳርፋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሀ ሀገራት ውስጥ ፍቺ
ልጆችን የጎዳና ተዳዳሪነት ድረስ ሲያደርስ ይታያል፡፡
----
2. በተፋቺዎቹ ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ
የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች በፍቺ ሲለያዩ
በራስ መተማመናቸው ይቀንሳል፣ በድብርት
ይጠቃሉ፣ከፍተኛ ለሆነ ጭንቀት ይዳረጋሉ፣የጤና መቃወስ
ያጋጥማቸዋል፣ ህይወትን ከዜሮ ለመጀመር
ይገደዳሉ………ወዘተ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ
ማህበረሰባዊነት በሚንጸባረቅበት አገሮች ውስጥ ደግሞ
ፍቺ ከተፋቺዎቹ አልፎ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎችንም ማለትም
ቤተሰቦቻቸውን ፣ ጓደኞቻቸውን….ወዘተ ለከፍተኛ የስነ
ልቦና ጫና የሚዳርግ ነገር ነው፡፡ እንዲሁም የተፋቱት
ሰዎች ቶሎ ለማገገም ሲቸገሩም ይታያሉ፡፡
----
ፍቺ ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር ነገር ከሆነ ሰዎች ለምን
ይፋታሉ?
የፍቺ ምክንያቶች እጅግ በጣም ብዙ ሲሆኑ ከሰው ሰው
የሚለያዩ ናቸው፡፡ሁሉንም ምክንያቶች መዘርዘር ባይቻልም
ያስተምራሉ ብዬ ያመንኩባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች
ከዚህ በታች አቀርብላችኋለሁ፡፡
---
1. ትዳርን ፍጹም ደስታ እንደሚገኝበት አድርጎ ማሰብ
ትዳር ለሰው ልጆች ደስታ የሚሰጥ ነገር ነው፡፡ነገር ግን
ከፍተኛ ሀላፊነትን መቀበልንም ይጠይቃል፡፡የጥናት
ውጤቶች እንዲያሳዩት ከሆነ ከትዳር ደስታን ብቻ
ለማግኘት አስበው የሚጋቡ ሰዎች የመፋታት እድል
አላቸው፡፡እናትና አባቶቻችን በትዳር ውስጥ 40 እና 50
አመት የኖሩት ደስተኛ ሆነው ብቻ አይደለም
የሚያጋጥማቸውን ፈተና በጽናት እያለፉም ጭምር ነው፡፡
----
2. አሁን እየተተካ ላለው ትውልድ አርአያ የሚሆኑ ሰዎችን
በደንብ አጉልቶ አለማውጣት
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከረኩት በአገራችን በትዳራቸው
ጸንተው ብዙ ችግሮችን አልፈው 40 እና 50 አመት መኖር
የቻሉ ብዙ አርአያዎች አሉን ነገር ግን የእነዚህን ሰዎች
ተሞክሮ ለቀጣዩ ትውልድ ከማድረስ አንጻር ብዙ
ተሰርቶበታል ብዬ አላምንም፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህን ሁሉ
አመት የኖሩት ደስተኛ ሆነው ብቻ ነው ወይስ በትዳራቸው
ለመቆየት ቁርጠኛ ስለሆኑም ጭምር? ልናቀው የሚገባ
ነው፡፡
አንዳንድ ሚዲያዎች እነዚህ ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ
የነቢዮነሴን የ3 ወር ትዳር ወይም የምራባውያንን የፍቺ
መጠን ማውራት ይቀናቸዋል፡፡በዚህ ላይ አለም አንድ
መንደር እየሆነች ባለችበት በዚህ ዘመን መረጃዎች
በቀላሉ ይገኛሉ በዚህ እና መሰል ምክንያቶች ማንን
አርአያ ማድረግ እንዳለበት ግራ የተጋባ ትውልድ
ይፈጠራል፡፡ከትዳር አንፃር የተሳሳተ አርአያ ያለቸው ሰዎች
ደግሞ ፍቺን አንድ የህይወት አማራጭ አርገው የማየት
እድል ይኖራቸዋል፡፡
---
3. ሌሎች ምክንያቶች
ለትዳር መፍረስ ምክንያቶች የሚሆኑ ብዙ ምክንያቶች አሉ
ለምሳሌ ታማኝ አለመሆን፣ መነጋገር አለመቻል፣ንብረትን
በጋራ አለማስተዳደር፣የትዳር አጋርን ስሜት አለመረዳት፣
ቅናት ፣የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት…………ወዘተን
መጥቀስ ይቻላል፡፡
---
ከላይ እነደማሳያ የጠቀስኩላችሁ የተወሰኑትን ምክንያቶች
ነው፡፡ በእናንተ አስተያየት ሰዎችን ለፍቺ እየዳረገ ያለው
ምክንያት ምንድን ነው? በትዳር ውስጥ ጸንቶ ለመቆየት
ምን ያስፈልጋል? ልንነጋገርበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ
ነው፡፡
--
በመጨረሻም በእውቁ የቤተ ክርስትያን አባት ዮሀንስ
አፈወርቅ አባባል ጽሁፌን ላጠናቅ
“ባልና ሚስት ልክ እንደ ዐይን እና እጅ ናቸው ዐይን
ሲያለቅስ
እጅ እንባውን ይጠርግለታል እጅ ሲታመም ዐይን
ያለቅሳል”፡፡
----=======================-----------------
@በሱፍቃድ ዜና የሰዎችን እድገት በሚያጠና የስነበሃሪ
ትምህርት ዘርፍ(Developmental psychology)
ሁለተኛ ዲግሪ(ማስተርስ) ያለው ሲሆን ባሁኑበልጆች
አስተዳደግ እና በትምህርት ዙሪያ ወላጆችን የሚያማክር
ድርጅት ከፍቶ በግሉ እየሰራ ያለ ወጣት ባለሙያ ነው ፡፡
ለበለጠ መረጃ zbesufekad@gmail.com
ሐሙስ 5 ሜይ 2016
ፍቺ
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ