ዓርብ 24 ሜይ 2019

ያለፉት አስር ወራት በወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 2.15 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው

ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ገፁ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳመለከተው በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ከግብርና፣ ከማኑፋክቸሪንግ እና ከማዕድን ምርቶች ዘርፍ በአጠቃላይ 3.51 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ በአፈፃፀም የተመዘገበው 2.15 (61.29%) ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡
ይህ አፈፃፀም ከአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 2.35 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ 196.47 (8.38%) ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል፡፡ 
በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ከተያዘላቸው ዕቅድ በላይ አፈጻጸም ያስመዘገቡት የወጪ ምርቶች ባህርዛፍ፣ ታንታለምና ጫት ናቸው፡፡ የዕቅዱን ከ75% እስከ 99% ክንውን ያስመዘገበ የምርት አይነት የጥራጥሬ ሰብሎች ናቸው፡፡
ከተያዘላቸው ዕቅድ ከ50% እስከ 74% ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች እንደቅደም ተከተላቸው የቅባት እህሎች፣ ኤሌክትሪክ፣ ቡና፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ አበባ፣ ሻይ ቅጠል፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና ሥጋ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ከተያዘው ዕቅድ አንጻር በውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ50 በመቶ በታች ዝቅተኛ ገቢ ያስመዘገቡ የወጪንግድ ምርቶች እንደቅደም ተከተላቸው ሰም፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ቅመማቅመም፣ ዓሳ፣ ማር፣ ምግብ መጠጥና ፋርማቲስቲካል፣ የስጋ ተረፈ ምርት፣ ሌሎች ማዕድናት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የቁም እንሰሳት፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ ወርቅ፣ የብዕርና አገዳ እህሎች እና ብረታ ብረት ናቸው፡፡
በበጀት ዓመቱ አስር ወራት 3.51 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ በአፈፃፀም የተመዘገበው 2.15 (61.29%) ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ይህን አፈፃፀም ጉድለት ለመሸፈን በቀጣይ ወራት ከፍተኛ የሆነ ስራ መሥራት እንዳለብን ያመለክታል፡፡
ግብርና ምርቶችን በተመለከተ በአንዳንድ ምርቶች የሚታየውን የአገር ውስጥ ግዢ ዋጋ ከዓለም አቀፉ ዋጋ ጋር ያለመጣጣምና ላኪዎች የገቡትን ኮንትራት ከገበያ ገዝተው ማሟላት ያለመቻላቸው ችግሮች መንስኤና መፍትሄዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላትና ከግብይት ተዋንያን ጋር በቅንጅት በመስራት የሚላከውን ምርት መጠን እንዲጨምር የማድረግና ከመሸጫ ዋጋ በታች (under invoice) በሚያስመዘግቡና በሚልኩ ላኪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እና የግብይት ተዋናዮችን በሚፈለገው ደረጃ በመደገፍ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች አፈፃፀምን ለማሻሻል በተለይም ዝቅተኛ ደረጃ አፈጻጸም ያስመዘገቡትን ድርጅቶች የሚስተዋሉባቸውን ውስጣዊም ሆነ ውጪያዊ ችግሮች እንዲፈቱ ድጋፍ በማድረግና እና የቅንጅት አሠራራችንን እንዲጠናከር በማድረግ አፈጻጸማቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ ይገባናል፡፡
የማዕድን ዘርፍን በተመለከተ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የኮንትሮባንድ ንግድን በጋራ መከላከል፤ የአምራቾችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረግ እና በተለያዩ ድንበር አካባቢዎች ያለውን የግብይት ሁኔታ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል፡
በአጠቃላይ በቀሪ ወራት ለኤክስፖርት አፈጻጸማችንን ለማሻሻል የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማትና የንግዱ ማህበረሰብ በጋራ ሊረባረቡ ይገባል፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ