ረቡዕ 9 ማርች 2016

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሴቶች ብቻ የሚመራውን ሁለተኛ በረራ ዛሬ ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ አደረገ።

ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረማሪያም የአለም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀውን ልዩ የበረራ ፕሮግራም ላይ እንዳሉት አየር መንገዱ ሴቶችን በሁሉም የስራ መስኮች በማሳተፍ የመሪነት ሚና ለመጫወት እየሰራ ይገኛል።
በአለም በአቬሽንና ሌሎች ስራዎች ሴቶች በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው በብዛት እንዲሳተፉ ግን ብዙ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
በተለይም በአፍሪካ በዘርፉ የሴቶች ተሳትፎ ወደ ኋላ መቅረቱን ጠቅሰው ከባህል ተጽእኖ ወጥተው በብዛት የሚሳተፉበትን ሁኔታ በመፍጠር ብዙ መስራት ይጠይቃል።
በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመሪነት ሚናውን ለመጫወት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የመጀመሪያው በሴቶች ሙሉ ለሙሉ የሚሰራ በረራ ወደ ታይላንድ ባንኮክ ከተደረገ በኋላ የዝንባቡዌና ኢንዲያ አየር መንገድ ተመሳሳይ በረራ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም አየር መንገዱ ለአለም መነሳሳትን እየፈጠረ ነው ብለዋል።
በአየር መንገዱ 32 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ በበረራ፤ ቴክኒሻንና ሌሎች ዘርፎች ቁጥራቸው እየጨመረ ሲሆን በሁሉም የስራ ዘርፍ እኩል ተዋጽኦ እንዲኖር ብዙ መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት።
በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመንም ወደ 50 በመቶ ለማድርስ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በረራው ወደ ሩዋንዳ የተደረገበት ምክንያትም አገሪቱ በፓርላማ ፤ በአመራርና ሌሎች የስራ ዘርፎች ሴቶችን በማሳተፍ ከአፍሪካ ቀዳሚ አገር በመሆኗ ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የስርአተ ጾታ እኩልነትና ሴቶችን ማብቃት በኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ሚስ ፈንሚ ባሎጉን በበኩላቸው አየር መንገዱ ሴቶችን ለማብቃት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
በቀጣይም በአህጉሪቱ የተቀናጀ ስራ በመስራት ሴቶች እኩል ተሳታፊ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል።
የአብራሪነት ሙያ ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ ሴቶች ደፍረው የማይገቡበት የነበረ ሲሆን አሁን በብቃት እየተወጡ ነው ያሉት ደግሞ በአየር መንገዱ በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ሴቶች ናቸው።
በበረራ አስተናጋጅነት ለ25 አመታት ያገለገሉት ወይዘሮ ፍልፍል ሙሉጌታ እንዳሉት ስራ በጀመሩበት ወቅት ሴቶች በብዛት የሚሳተፉት በበረራ አስተናጋጅነት እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን በአብራሪነትና በሌሎችም የስራ መስኮች በመሳተፍ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት እየተወጡ ነው ብለዋል።
የአውሮፕላን ጥገና ዋና አስተባባሪ የሆኑት ወይዘሮ እታገኝ ሁነኛው በበኩላቸው በበረራዎች በሴቶች ብቻ መደረጋቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት ራሳቸውን ችለው እንዲሰሩ የሚያደርግና ችሎታቸውን የሚያሳዩበት በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል ብለዋል።
ወደ ፊትም ሴቶችን በብዛት በማሳተፍ አየር መንገዱ ቢሰራ የተሻለ ውጤት ሊያስመዘግብ ይችላል ነው ያሉት።
ኢዜአ፣ የካቲት 29/2008

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ