‹‹… ምኒልክ ዘመናዊ ትምህርት ቤትን በመክፈት በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የትምህርት ዘር የዘሩ ናቸው:: ትምህርት ቤቱም የተሠራው ንጉሠ ነገሥቱ በሰጡት የግል ገንዘብ ነው:: …››:: በአገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት በ19ኛው መቶ ዘመን በነገሡት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በአሁን ዘመን ዳግማዊ ምኒልክ ተብሎ የሚጠራውና ዘመናት የተሻገረው ተቋም መቋቋሙ ይወሳል:: በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው የፕሮፌሰር ጆን ማርካኪስ አገላለጽ ሌሎች የታሪክ ምሁራንም ይጋሩታል:: በፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ድርሳን አገላለጽም፣ የመደበኛ ትምህርት በኢትዮጵያ ለመስፋፋት እንደ አንድ ዐቢይ ክስተት የሚቆጠረው ድርጊት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተከናወነው በንጉሠ ነገሥቱ ስም የሚታወቀው ትምህርት ቤት በ1900 ዓ.ም መከፈቱ ነው:: ‹‹የዘመናዊ ትምህርት›› ፍላጎት እያደገ መምጣት የጀመረው በ19ኛው መቶ ዓመት መሆኑን ከዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ከአውሮፓና ከአውሮፓውያን ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ ሲሄድ ዘመናዊ ትምህርት ለማስፋፋት አመቺ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የታሪኩ ድርሳን ያመለክታል::
ይሁን እንጂ ነባሩ የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት የሚጀምረው ግን በዘመነ አክሱም ከአራተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ መሆኑም ይገለጻል:: የተለያዩ ጸሐፍትና የሥነ ትምህርት ምሁራን ነባሩን የትምህርት ሥርዓት ባህላዊ የትምህርት ሥርዓት፣ የቤተክህነት ትምህርት ቢሉትም ደስታ በርሀ ስብሐቱ በአንድ ጥናታቸው እንዳመለከቱት፣ነባሩ የትምህርት ሥርዓት ‹‹የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት›› መባል አለበት ይላሉ::›› ለዚህም ማገናዘቢያቸው እስከ 20ኛው መቶ ዓመት መባቻ ድረስ የኢትዮጵያ ትምህርት በተማከለ ወይም ባልተማከለ መልኩ በተለያዩ አካላትና ተቋማት አስተዳደርና ሥር መከናወኑ ነው:: በ19ኛው መቶ ዓመት መገባደጃ ከዘመናዊነት ጋር የተያያዙ ባቡር፣ ሆስፒታል፣ ባንክ፣ መኪና ወዘተ. በኢትዮጵያ መከሰትን ተከትሎ ከውጭ አገሮች ጋር ከተፈጠረው ግንኙነት አኳያ ዘመነ ምኒልክ ብዙ ትሩፋቶችን አስገኝቷል::
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ