ሐሙስ 10 ማርች 2016

የሌሊት ወፍ !


‹‹ ወፍ ናት›› በምል  ጊዜ ‹‹ አጥቢ ናት›› ይሉኛል፣
‹‹ አጥቢ ናት›› እንዳልል  ስትበር   ይታየኛል፡፡
ቀን  ያስቀይማታል፣ ብርሃን ያስጠላታል፤
የሌት  ወፍዋ  ምስጢር እንደምን  ይፈታል?
ምን  አይነት  እርግማን፣ ምን  አይነት  ተፈጥሮ !
ከብርሃን  ተጣልቶ፣ ከሌሊት  ተፋቅሮ፣
ተዘቅዝቆ  ማደር ! ተዘቅዝቆ  ኑሮ፡፡
በቁንጽል ሃሳቤ ምስጢሩን  ለማወቅ ትንሽ መረምር፣
ብዙ…! ብዙ ብጥር፣
ሊገባኝ  አልቻለም፤ ማሰሪያዉ፣ መቁዋጫዉ  የዚህ  ዉትብትብ ድር፤
ተፈጥሮ  ግሩም  ናት ! ድንቅ ናት ተአምር !
አንዱን መሬት ጠቦት በጣም  ተሞላቆ፣
በጣም ተንደላቆ!
ሌላዉ ግን…
ቀና  ማለት እንኩዋ  ባያሌዉ ተስኖት  ሊኖር  ተዘቅዝቆ፣
ዉድቆ በኖረባት ጉስቁል  መሬት  ላይ  ሲቀር የትም  ወድቆ፣
 ‹‹ ህይወት›› የሚባለዉ  መራራ ነዉ በጣም ! ሬት  ነዉ  እንቆቆ
በዚህ  ስሌት  ሲታይ  ሲመረመር  ጣጣዉ፣ ጎባጣዉ፣ ገጣጠዉ፣
የወፍዋና ያንተ  ኑሮአችሁ አንድ ነዉ፤ አንድነዉ የት መጣዉ፡፡
 የወፍዋና ያንተ  ኑሮአችሁ አንድ ነዉ፤ አንድነዉ የት መጣዉ፡፡
ቀን  ፊቱን  ነስቶዋቸዉ፣ ጨለማ  ዉጦዋቸዉ፣ የትም  ባካኞቹ፣
ወሽክሬ ኑሮን፣ ምስቅልቅል ህይወትን  ሁሌ ገፊዎቹ፤
አፈር እየጋጡ፣ ቁልቁል እየኖሩ ‹‹ ተመስገን›› ባዮቹ፣
በደንብ  ካስተዋልኸዉ እኔና  አንተ'ኮ ነን  የሌሊት ወፎቹ፡፡
 ምንጭ ካነበብ ነው(አበራ አዳሙ
ውዳሴ ሞት የግጥም መድበል)


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ