ሰኞ 19 ፌብሩዋሪ 2018

ህጉን ተፈጻሚ ለማድረግ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል

አገሪቱ ሲጋራ ማጨስ መቆጣጠርን አስመልክቶ የትንባሆያጸደቀቻቸውን አለም አቀፍ ኮንቬንሽን እንዲሁም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ የወጣውን የማስፈጸሚያ አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሀኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣኑ የህግ ክፍል ዳይሬክተር ወይዘሮ አብረኸት ግደይ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተ ናገሩት፤ ትምባሆን መጠቀም እንደ አገር ጎጂ በመሆኑ ምርቱ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል። አገሪቱ ያጸደቀችውን ዓለም ዓቀፍ ኮንቬንሽን ወደ ተግባር ለመቀየርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አወጅ ቁጥር 822/2006 ተፈጻሚ ለማድረግ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሀላፊነት ተሰጥቶታል።
የቁጥጥር ስራው በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ብቻ ተሰርቶ ውጤታማ እንደማይሆን ዳይሬክተሯ ጠቅሰው፤ የሚመለከታቸው የዘርፍ መስሪያ ቤቶችና የክልል መንግስታት በተለይም የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ህጉን ተፈጻሚ ማድረግ ዋና ስራ ቢሆንም ከዚህ ጎን ለጎን ግን የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማዳበር ስራ መሰራት አለበት፤ አመዛኙ ስራም መከናወን የሚገባው በዚህ ደረጃ ነው፡፡
የትግራይ ክልል ከዚህ አንጻር ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው፤ ክልሉ በምርጥ ተሞክሮው የአለም ጤና ድርጅት ጭምር የመሰከረለት መሆኑን ገልጸዋል፤ ክልሉ ለእዚህ ውጤት የበቃው የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስፋቱና በስራው ላይም ተሳትፎ እንዲያደርግ ሁኔታዎችን በማመቻቸቱ መሆኑን አስረድተዋል።
በዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በዓመት ሰባት ሚሊዮን ህዝብ ከማጨስ ጋር በተያያዘ ህይወቱን ያጣል።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ