ዓለም አቀፉ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አውደ ርዕይ በሚቀጥለው ወር በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማኅበር አውደ ርዕዩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
አውደ ርዕዩ 'ሆርቲ ፍሎራ ኤክስፖ 2018' በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል።
በአውደ ርዕዩ ላይ ለመሳተፍ 120 የአገር ውስጥና የውጭ አምራቾች፣ ግብዓት አቅራቢዎች፣ አማካሪዎች፣ ገዥዎችና ባለድርሻ አካላት መመዘገባቸው ተገልጿል።
ለሦስት ቀናት ከሚካሄደው ከዚህ መርሀ ግብር ጎን ለጎን የቢዝነስ ስብሰባዎች፣ የሚመለከታቸው አካላት የሚሳተፉበት አውደ ጥናቶችና የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እርሻ ልማት ሥራዎች ይጎበኛሉ ተብሏል።
የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ እንደገለጹት፤ ኢንዱስትሪው ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ በፍጥነት እያደገ መጥቷል።
ኢትዮጵያ አበባን ወደ ውጭ በመላክ ከአፍሪካ 2ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጸው፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ወደ ወጪ ንግድ በመቀየር የሚጠበቀው ገቢ እንዲገኝ ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ እየሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ የውጭ መዳረሻዎች ያሉት በመሆኑ፤ ለማምረት ምቹ የሆነ የአየር ንብረት መኖሩ፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አገልግሎት መጀመሩ ለሚጓጓዘው አትክልትና ፍራፍሬ "ትልቅ እመርታ ነው" ብለዋል።
ከአውስትራልያ፣ ከጃፓን፣ ከአሜሪካ፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአፍሪካ አገሮች በአጠቃላይ ከ40 አገራት በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች በአውደ ርዕዩ ላይ እንደሚሳተፉ አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።
የአውደ ርዕዩ መካሄድ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ከማሳየት ባለፈ አገሪቷ በመስኩ ተሰማርተው የሚገኙ ኩባንያዎች ልምድ እንዲቀስሙ እድል እንደሚፈጥርም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባለፈ በመንግሥት የተለዩ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ቦታዎች ለዓለም አቀፉ ተዋንያኖች ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
የተለያዩ አበባዎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች፣ ቴክኖሎጂዎች እንደሚቀርቡ ጠቅሰው፤ ክልሎችም በመስኩ ያላቸውን የኢንቨስትመንት አማራጮችን በስፋት ያስተዋውቃሉ።
የኃይል መቆራረጥ፣ አንዳንድ አሰራሮች መጓተት፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማነስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዳንሆን እየደረገ በመሆኑን ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
አውደ ርዕዩ ለ7ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከየካቲት 7 እስከ 9 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል።
sourse : ENA

ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ