ማክሰኞ 2 ጃንዋሪ 2018

በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች እየተሠሩ ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአ ንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ አራት ዕቃ ጫኝ  ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ውል ገብቶ እያሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የአየር መንገዱ የካርጎ ከፍል ዋና ሃላፊ  አቶ ፍጹም አባዲ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ  በብድር በተገኘ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር ወጪ  እያንዳንዳቸው በአንድ ጊዜ 103 ቶን ዕቃ የመጫን አቅም ያላቸው አራት  አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ውል ፈጽሟል፡፡
አራቱ ቦይግ 777 ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ባንኮችና አበዳሪ ድርጅቶች በተገኘ ብድር የሚገዙ  መሆናቸውን  ጠቅሰው፤ የአውሮፕላኖቹ  ግንባታ ተጠናቆ ቅብ ደረጃ በመድረሳቸው ከመ ጪው ዓመት መስከረም 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ ብለዋል፡፡
የደንበኞችን ፋላጎትና የካርጎ አገልግሎቱን ለማጣጣም አየር መንገዱ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተው፤ አዳዲሶቹ  አውሮፕላኖችም የአገሪቱን የወጪና የገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡
አዲሶቹ አውሮፕላኖች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የአየር መንገዱን የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ቁጥር ወደ 12 እንደሚያሳድገው ጠቁመው፤ አየር መንገዱ ከሚያጓጉዛቸው ዕቃዎች መካከል በዋነኝነት የአበባ ምርትን ጨምሮ የግብርና ምርቶች፣ ጨርቃጨርቅና የተለያዩ  የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችና የመኪና መለዋወጫዎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል አየር መንገዱ በአሁኑ ጊዜ በዓመት 350 ሺ ቶን  ዕቃ  የሚያስተናግዱ መጋዝኖች እንዳሉት ገልጸው  በ150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በዓመት 600 ሺ ቶን ዕቃዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው መጋዘን አስገንብቶ ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ ይህም  የካርጎ አገልግሎቱን የተሻለ እንደሚያደርገው ነው የገለጹት፡፡
በአሁኑ ጊዜ አየር መንገዱ ከ100 ቶን በላይ አቅም ያላቸው ዘመናዊ ስድስት ቦይግ 777 የሚባሉ አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፤ በጥቅሉ የስምንት ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡ በእነዚህም አውሮፕላኖች ወደ 44 መዳረሻዎች በመብረር በዓመት 400ሺ ቶን ዕቃዎችን ያጓጉዛል፡፡
አዲስ ዘመን (ጌትነት ምህረቴ)

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ