በሙከራ ምርት ላይ የቆየው የመሊ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ መደበኛ ምርት ጀመረ።
ፋብሪካው የሚገኝበት በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን በአስገደ ፅምብላ ወረዳ ሲሆን፥ በ1999 ዓ.ም በውጭ አገር አማካሪ ድርጅት ተጠንቶ በ2004 ዓ.ም ህጋዊ የስራ ፈቃድ ማግኘቱን ተነግሯል።
የትእምት እህት ኩባንያ በሆነው ኢዛና ማዕድን ልማት ኩባንያ ስር የሚገኘው መሊ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ፥ በአሁኑ ወቅት በቀን ከሁለት እስከ ሶስት ኪሎ ግራም ወርቅ እያመረተ መሆኑን የፋብሪካው ዋና ስራ አስከያጅ አቶ ፀጋይ አሰፋ ገልፀዋል።
ፋብሪካው በቀጣይ አቅሙን በማሳደግ እስከ 4 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም በቀን ለማምረት እቅድ መያዙንም ዋና ስራ አስከያጁ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በፋብሪካው ከ200 በላይ ዜጎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩም ተጠቁሟል።
የፋብሪካው ምክትል ስራ አስከያጅ እና የጂኦሎጂ ባለሙያ አቶ ወንድወሰን አረጋኸይ፥ ወርቅ ባለበት ቦታ 600 ሜትር ስፋት ያለው ቁፋሮ ለማድረግ የሚያስችል ጥናት መደረጉን ገልፀዋል።
ከዚህም እስከ አሁን ስድስት ሜትር አካባቢ ተቆፍሮ ወርቅ በማንጠር ላይ ነው ሲሉ አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል።
ፋብሪካው በ2010 ዓ.ም ለሀገሪቱ ከ40 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
(ኤፍ.ቢ.ሲ)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ