"ደህና ናችሁ ልጆች? የዛሬ ኣበባዎች የነገ ፍሬዎች
እንደምን ኣላችሁ ልጆች? ኣያችሁ ልጆች የኢትዮጲያ
ቴሌቭዥን የልጆች ግዜ ዝግጅት ክፍል እናንተን
ለማስደሰት ልክ በሰአቱ ይገኛል፥ እናንተስ ዝግጁ ናችሁ?
ኣዎዎ ኣባባ ሸንተረሩን ኣቋርጠው ዳገቱን ወጥተው
ቁልቁለቱን ወርደው በጓሮ በኩል ዲ ዲ ዲ ከተፍ ሲሉ
እናንተ ደሞ ቆማችኋል ኣይደል? በጣም ጥሩ ነው ልጆች፥
ኣንድ ኣባት ሲመጣ ብድግ ብሎ በኣክብሮት መቀበል
ኣስፈላጊ መሆኑን ሁልጊዜ እነግራችሁ የለም? ኣዎዎ በቃ
አሁን ተቀመጡ እንዳትጋፉ ታዲያ ትንንሾች ወደፊት
ትልልቆች ወደኋላ ኣዎዎ"
ሰኔ 20/1916 ዓ.ም በቀድሞዋ ባሌ ክፍለ ሃገር ከዶ
የተሰኘ አካባቢ ኣንድ ጀግና ፈለቀባት፥ ብላቴናው 14
ዓመት ሲሞላው ወደ ሸገር መጣ ከዚያም በኮከበ ፅባህ
ኣስኳላ ትምህርቱን መከታተል ጀመረ።
በኣንድ ወቅት የኣዲስ ኣበባ መስተዳደር ባህል እና ቲያትር
ኣዳራሽ ማስታወቂያ ሲወጣ በተዋናይነት ተመዝግቦ
ተቀጠረ፥ በወቅቱ ሴት ልጅ ወደ ማጀት እንጂ ኣደባባይ
ላይ መዋል ነውር ነበርና ለትወና የምትመጣ ሴት
ኣልነበረችም እናም ይህ ሰው የሴቶችንም ገጸባህሪ
ወክሎ በብቃት ይጫወት ጀመር። እንዲያውም ኣንድ
ወቅት ላይ ኣንድ ትያትር ሊያይ የገባ ሰው "ይህቺን ሴት
ወድጃለሁ" ብሎ ኣምባጓሮ እስኪፈጠር መስሎ ሳይሆን
ሆኖ የሚተውን እሳት ተዋናይ ነበር፥ ለዚህም
- ‘ሀ ሁ በስድስት ወር’
- ‘ኤዲፐስ ንጉስ’
- ‘አሉላ አባነጋ’
- ‘ዳዊትና ኦርዮን’
- ‘ኦቴሎ’
- ‘አስቀያሚዋ ልጃገረድ’
- ‘ስነ ስቅለት’
የተሰኙ እሱ የተጫወተባቸው ተውኔቶች ዉስጥ የሚጠቀሱ
ናቸው፥ ይህ ሰው ወደ ድርሰቱ ኣለም ገብቶም
- ‘ብጥልህሳ’
- ’ ነው ለካ’
- ‘ጠላ ሻጯ’
የተሰኙ ተውኔቶች ኣበርክቶ ግዙፍ ኣሻራውን ያሳረፈ ሲሆን
በተጨማሪም አራት የተረት መጻሕፍት ለልጆች ኣድርሷል።
በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም ደግሞ
"የልጆች ግዜ" የተሰኝ ፕሮግራም እንዲኖር ሃሳቡን አቅርቦ
ሲፀድቅለት እስካሁንም ማንም ሊተካው ባልቻለና የእርሱ
ብቻ በሆነ የአቀራረብ መንገድ በመጠቀም ለመላው
የኢትዮጲያ ህዝብ ለ42 ዓመታት ያህል በኣባትነት ስሜት
ኣቅርቧል።
ለልጆች ብቻ ሳይሆን ለኣዋቂም የሚሆኑ ወዝ ያላቸው
ቁምነገር ኣዘል ተረቶችን፣ ጨዋታዎችን እና ኣስተማሪ
ዝግጅቶችን እያደረሰ መልካም ማንነትን የተላበሰ ትውልድ
ለመገንባት መተኪያ የሌለው ኣስተዋፅዖ እና ድርሻ
ኣበርክቶልናል።
ኣባባ ተስፋዬ እንኳን ለ93ኛ ዓመት የልደት በዓልዎ
ኣደረሰን፥ ውለታዎ ብዙ ነው ትውልዶች ሁሉ ሲያከብርዎት
ይኖራሉ እርስዎ በተለያየ ዘመን ውስጥ፥ በኣስቸጋሪውም
በጥሩውም የሀገር ሁናቴ በሚልየን ለሚቆጠሩ የኢትዮጲያ
ልጆች ስለ ሐገራቸው እንዲታስቡ መምህር የሆኑ
የትውልድ ኣባት ነዎትና እናከብርዎታለን፡፡ እንደ ትላንቱ
ሁሉ ሁሌም እርስዎን ስናስብ ከመቀመጫችን ብድግ
ብለን ልናከብርዎት የውዴታ ግዴታችን ነው። ከዛሬ ጀምሮ
የሚታሰብ ከእኔ እድሜ ተቆርጦ ለእርስዎ ለኣባቴ ቢሰጥ
እወዳለሁ
ልጅዎ
ምንጭ: Getu Temesgen - (ጌጡ ተመስገን)
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ