ዓርብ 3 ጁን 2016

ዳጉ፤ አስደናቂው የአፋሮች የመረጃ ልውውጥ እሴት፤=====================================

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ
ፍለጋው ወደ አፋር እየወሰደን ነው፡፡ የአፋርን አስደናቂ
መስህቦች ከመጎብኘታችን በፊት ስለ ዳጉ ማወቅ አለብን
ይላል፡፡ ዳጉ ካለን አፋርን እንዲህ እንጎበኘዋለን፡፡)
(ሔኖክ ስዮም በድሬትዩብ)
የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ፍለጋችንን ከዚህ በላይ
አንገፋበትም፡፡ ወደ አፋር ምድር ጉዞአችንን ቀጥለናል፡፡
ሱልጣኑ እንደአሉት እንኳን አፋሮች ግመሎቻቸው
የአንድነታችን መገለጫዋን ባንዲራችንን ያውቋታል፡፡
ወደዚህ ምድር እየሄድን ነው፡፡
አምስት ዞን 31 ወረዳና አንድ ልዩ ወረዳ የፈጠሩት
የአፋር ክልል 96,256 ስኩዬር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋትን
ይሸፍናል፡፡ በታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ
ውስጥ ያረፈው አፋር ምድር ከባህር ጠለል በታች እስከ
116 ሜትር የሰረጎዱ ሸለቆዎች የሚገኙበት ሲሆን ሙሳ
አሊ ከባህር ጠለል በላይ 2063 ሜትር የሚዘረዝመው
አፋር ትልቁ ተራራ ነው፡፡
አዋሽ ከተማ ቆመናል፡፡ አዋሽ ሰባት ኪሎ በሚለው
መጠሪያዋ ትታወቃለች፡፡ ከኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መቆም
ጋር ተያይዞ ደማቋ ከተማ ለዓመታት ፈዝዛ ኖራለች፡፡
አሁን አዋሽ ባቡሩ ጀመረ እንዴ የምታስብል ከተማ
እየሆነች ነው፡፡
መንገድ አንጀምርም፤ ከዚያ በፊት ዳጉ ያስፈልጋል፡፡ ዳጉ
የአፋሮች ቁልፍ እሴት ነው፡፡ አፋር ከዘመን ቀድሞ
የመረጃን ፋይዳ የተገነዘበ ህዝብ ነው፡፡ መረጃን በፍጥነት
የሚለዋወጡበት እሴት ዳጉ ይባላል፡፡ ያለ ዳጉ ህይወት
የለም፡፡ የአፋሮች ዳጉ ፈጣንና እውነተኛ ነው፡፡ ተአማኒነቱ
የተለየ መገለጫው ሲሆን በፍጥነትም ወደር የለውም፡፡
ቡሬሙዳይቱ የተከሰተው ሳይረፍድ ኤሊዳር ይሰማል፡፡
ማንዳ የተከወነው ሳይዘገይ አፍዴራ ይገባል፡፡ ሙሳ አሊ
የተወራው አዘሎ ሲደርስ ደከመኝ ብሎ መንገድ ሳያድር
ነው፡፡ ከበርሐሌ ዱብቲ፣ ከአሳኢታ ሚሌ ዳጉ ፈጥኖ
የሚደርስ የመረጃ መለዋወጫ ስልት ነው፡፡ ፍጥነቱ
የደወሉላቸው ደንበኛ ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ
ናቸው ከሚለው የስልካችን አገልግሎትም የሚፈጥንበት
ጊዜ አለ፡፡
የአፋሮች እንቅስቃሴ በዳጉ የተደገፈ ነው፡፡
ስለሚደርሱበት አካባቢ በቂ መረጃ በየደረሱበት
ይሰማሉ፡፡ ስለአለፉባቸው አካባቢዎች ደግሞ
ለደረሱባቸው ስፍራዎች አስተማማኝ መረጃ ይሰጣሉ፡፡
ይሄ ከማህበራዊ ትስስራቸው ባሻገር የኢትዮጵያን ድንበር
ሳትደፈር ተከብራ እንድትኖር በጽናት እንዲጠብቁ
ያስቻላቸውን ብቃት የፈጠረ እሴት ነው፡፡
አዋሽ ሰባት ቆመን ዳጉ እንሰበስባለን፡፡ ከዚያ ጉዞው
ይቀጥላል፡፡ የአዋሽ አርባን ሙቀት እንጋራዋለን፡፡ በመተካ
ፍል ውሐዎች እንጠበላለን፡፡ የአፋር ምድር አማካይ
የሙቀት መጠን ዝቅ ሲል 18 ከፍ ሲል 45 ዲግሪ
ሴንቲግሬድ ይደርሳል፡፡ እንደ ምድሩ እንለብሳለን፡፡
ጉዞአችን ወደ አፋሮች ምድር ነው፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ